“ዓብይ ጾም እና በገና ምን አገናኛቸው?”
ይህ ጥያቄ በተለያዩ ቃለመጠይቆች እና በማህበራዊ ሚዲያ መስተጋብር ብዙ ጊዜ የምንጠየቀዉ ጥያቄ ነው። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የዐቢይ ጾምን ማንነት እና የበገናን ተፈጥሮ እንዲሁም ከእነዚህ ትስስሮች በስተጀርባ ያለውን ታሪክ መመልከት ያስፈልጋል።
በግላዊ ተመስጦ መፈለግ
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዐብይ ጾም ጊዜ የጾምና እግዚአብሔርን የመሻት ጊዜ ነው። ራስን መመርመር እና መጾም ፣በምግብ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ስሜቶች እና አካላቶች ያስፈልጋል። ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ሲል ያስተምራል
"ጆሮ ከሚሰማው ይጹም፥ አፍ የሚናገረውን ይጹም አይኖችም የሚያዩትን ይጹሙ"
የበገና ተፈጥሮም ከአብይ ጾም ትምህርት ጋር ተመሳሳይ ነው። በገና እግዚአብሔርን ለማምለክ ብቻ የምንጠቀመዉ መንፈሳዊ መሳሪያ ነው። በገና ሌላ አጋዥ መሳሪያዎች አያስፈልገውም። የበገና መዝሙሮች፣ ግጥሞች ጥልቅ ራስን መርማሪ ናቸው። ስለዚህም በገና ትልቅ የአምልኮ መሳሪያ እና ለዐቢይ ጾም የሚሆን የመንፈሳዊ ጸሎት መሳሪያ ነው።
የበገና ታሪክ በዐብይ ጾም
በታሪክ በኢትዮጵያ የንጉሠ ነገሥት ዘመን የሬዲዮ ጣቢያዎች በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ መሠረት የበገና መዝሙር ብቻ ይጫወቱ ነበር። ይህም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ትልቅ ተፅዕኖን ጥሏል። በዛን ጊዜ ያደጉ ልጆች በገናንና ዐቢይ ጾምን ያቆራኙታል። በተጨማሪም የባህል ዘፋኞች በዚህ የፆም ወቅት ከዘፈንና ከዘፋኝነት ይቆጠባሉ፣በዚህም ምትክ የበገና መዝሙሮችን እንደ (መዲና እና ዘለሰኛ) የመሳሰሉትን በበገና፣ በክራር እና በመሰንቆ ይዘምራሉ።
ጊዜ የማይሽረው መሣሪያ
በገና ግን የምንጊዜም መሳሪያ ነው፣ ሁልጊዜ የሚያስፈልግ መሳርያ ነዉ። የመንፈስ ጭንቀት እና የተለያዩ የአእምሮ ሕመሞችን ፈዋሽ የሆነ መንፈሳዊ መሳሪያ ነው.
“ምግብ ለዕለት ተዕለት ኑሮ እንደሚውል ፣ ነገር ግን በተለያዩ በዓላትና ጊዜዎች የምግቡ ዓይነት እንደሚለዋወጥ ሁሉ ፣ በገናም የዕለት ተዕለት መሣሪያ ነው። ግጥሙ እና ዜማዉ በጊዜና በሁኔታዎች ሊለዋወጥ ይችላል ፤ ቢሆንም በገና የዕለት ተዕለት መሳሪያ ነው።”
- ኤርሚያስ ኃይለይ
በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት በገና የጸሎታችሁን ህይወት እንዲረዳ እንድትፈቅዱ እና ወደ መንፈሳዊ እድገት እንዲመራችሁ እንጋብዛቹሀለን።
በዚህ የዐብይ ጾም ሳምንት (ዘወረደ) ለመስማት የበገና ሊቃውንት ዝማሪዎች መርጠን እንጋብዛችሁ።
መዲና እና ዘለሰኛ፡ መጋቢ ሥብሀት አለሙ አጋ
እስመ ላንተ፡ ዘርፉ ደምሴ
ግዱን ፡ ስዩም መንግስቱ
ዘወረደ፡ ኤርሚያስ ሃይለይ